FOR IMMEDIATE RELEASE
ወንጌል ታመነ፣ ህዝብ ግንኙነት እና የትብብር ስራ አስኪያጅ
0923591221
wongel.tamene@esx.et
የኢትዮጵያ ሰነደሙዓለ ንዋዮች ገበያ የካፒታልማሰባሰብ ጉዞውን ከታቀደው በላይ ካፒታል በመሰብሰብ በይፋ አጠናቋል። ሰፊ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ ታይቷል።
የኢትዮጵያ ሰነደሙዓለ ንዋዮች ገበያ ካቀደዉ ካፒታል በላይ መሰብሰብ ቻለ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮዮጵያ- መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ (“ገበያ” ወይም “ገበያው”) ሥራ ለመጀመር ያስፈልገኛል ብሎ ካቀደው ከሁለት እጥፍ በላይ የሆነ ተሳትፎን በማሳካት ካፒታል የማሰባሰብ ሂደቱን ማጠናቀቁን በዛሬው ዕለት አሳውቋል። በህዳር ወር 2016 ዓ.ም የተጀመረው ይህ በገበያው የሥራ አመራር አባላትና በአማካሪዎቹ ብርቱ ጥረትና በአዲስ አበባ፣ ናይሮቢና ሎንዶን በተደረጉ ባለሀብቶችን የማግባባትና የማሳመን ሥራዎች ከሀገር ውስጥና ከውጪ ባለሀብቶች ከተጠበቀው በላይ የሆነ ምላሽን በማግኘት በድምሩ ብር 1.5 ቢሊየን (26.6 ሚሊየን ዶላር) ካፒታል ማሰባሰብ ችሏል። ይህም በመጀመሪያ ከታቀደው የብር 631 ሚሊየን (11.07 ሚሊየን ዶላር) ካፒታል በ240% የሚበልጥ ሲሆን በድምሩ 48 በፋይናንስና ከፋይናንስ ዘርፍ ውጪ ባሉ ዘርፎች የተሰማሩ ተቋማዊ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ተሳትፎ አድርገዋል።
ገበያው ግንባር ቀደም በሆነ የግልና የመንግስት አጋርነት በጥቅምት 2016 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን መንግስት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል የ25% የተፈቀደ ካፒታል ድርሻ ሲይዝ የግል ዘርፉ ደግሞ ቀሪውን 75% ድርሻ ይዟል።
በዚህ ዕለት ገበያው የድርሻ ተሳትፎ ያደረጉት ተቋማት እንደ ኤፍ.ኤስ.ዲ አፍሪካ፤ የትሬድና ዴቨሎፕመንት ባንክ ግሩፕ (ቲዲቢ) እና የናይጄሪያ ኤክስቼንጅ ግሩፕ (ኤን.ጂ.ኤክስ ግሩፕ) ያሉ የውጭ ባለሀብቶችንና ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ደግሞ 16 የግል የንግድ ባንኮችን፤ 12 የግል የኢንሹራንስ ድርጅቶችን እና 17 ሌሎች የሀገር ውስጥ ተቋማዊ ባለሀብቶችን ያካተተ ነው። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስና እንደ ኢትዮቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሉ ኩባንያዎች በድምሩ የ25% ድርሻ ካላቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል የሚካተቱ ናቸው።
ካፒታል የማሰባሰብ ሂደቱ እስከሚጠናቀቅ ባለው ጊዜ የታየው ከፍተኛ ፍላጎትና መረባረብ ኢትዮጵያ እያካሄደች ላለው የፋይናንስ ዘርፍ ልማትና የኢኮኖሚ ለውጥ የገበያው ተግባራዊነት ለሚያበስረው አዲስ የስኬት ጉዞ በባለሀብቶች በኩል ያለውን ከፍተኛ እምነትና ድጋፍ የሚያሳይ ነው። የካፒታል አሰባሰብን በማሳለጥ፣ ግልጽነትን በማጎልበትና የድርጅቶች መልካም አስተዳደርን በማበረታታት ገበያው አዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የመፍጠር፣ የስራ ፈጣሪነትን የማበረታታና በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ዘላቂ ልማትን የማስፋፋት ዓላማን አንግቧል።
የገበያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ጥላሁን እስማኤል ካሳሁን “የካፒታል ማሰባሰብ ሥራችን ከጠበቅነው በላይ የተሳካ በመሆኑና በኢትዮጵያ የሰነደሙዓለ ንዋዮች ገበያና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ዕድሎች ላይ ባለሀብቶች ባሳዩት እምነት ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል” ብለዋል። “በተለይ በቲዲቢ፣ በኤፍ.ኤስ.ዲ አፍሪካና በኤን.ጂ.ኤክስ ግሩፕ የተደረጉት ስትራቴጂካዊ የውጭ ኢንቨትመንቶች የቴክኒካል እውቀት ሽግግርንና የምርጥ ተሞክሮዎች ልውውጥን ለማግኝት እና ሌሎችንም የረጀም ጊዜ ስትራቴጃዊ ትስስሮችን እና እሴቶችን በመፍጠር ረገድ በእጅጉ ጠቃሚይሆናሉ” ሲሉም አክለዋል።
በተጨማሪም ዛሬ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያው በመጪዎቹ ወራት ወደሥራ ለማስገባት ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ እና ዋና ዋና ስራዎቹን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገበያው ይፋ አድርጓል። ከእነዚህ ተግባራት ውስጥም የገበያውን ሕገደንብ ለሕዝብ አስተያየት ይፋ ማድረጉ፣ ግብይትን ተግባራዊ ለማድረግ ቁልፍ የሆነውን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት አቅራቢ ድርጅቶች የቴክኒክ ግምገማ ማጠናቀቁና የኢንቨስተሮች የትምህርት ማዕከልን ለማቋቋም እየሰራ መሆኑ የሚጠቀሱ ናቸው።
############
የኢትዮጵያ የሰነደሙዓለ ንዋይ ግብይት በኢትዮጵያ መንግስትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የተቋቋመ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ነው። የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዓላማው የኢኮኖሚ ዕድገትን ማሳለጥ፣ የፋይናንስ አካታችነትን ማበረታታት እና ለኢትዮጵያውያን ጥሪት/ሀብት መፍጠር ነው። ድርጅቶች ካፒታል የሚሰበስቡበትን መድረክ በመፍጠር፣ የኢንቨስትመንት ዕድል በማመቻቸትና የድርጅቶች መልካም አስተዳደርና ግልጽነትን በማበረታታት ገበያው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የለውጥ ጉዞ ጉልህ ሚና ለመጫወት ዝግጁ ነው።