FOR IMMEDIATE RELEASE

ወንጌል ታመነህዝብ ግንኙነት እና የትብብር ስራ አስኪያጅ

0923591221

wongel.tamene@esx.et

ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ትምህርት ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ፡ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ ድጋፍ የአካዳሚ አገልግሎቱን አስጀመረ፡፡

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ ከኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ ጋር የፋይናንሺያል ሴክተር ትምህርትን ለማሳደግ አብሮ መስራት

አዲስ አበባ፣ ኢትዮዮጵያ- ታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ምህዳር ፈር ቀዳጅ የሆነ የኢንቨስተር ትምህርት፣ የፋይናንስ እውቀትን እና የካፒታል ገበያ ተሳታፊዎችን አቅም የመገንባት እና የማዳበር ስራዎችን የሚሰራ በሀገራችን ብቸኛ የሆነውን አካዳሚ ማስጀመሩን በኩራት ያበስራል፡፡ በኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ የተደገፈ እና ከሚኤላ ቴክኖሎጂ ኃ.የተ.የግ.ማ ጋር በመተባበር የተገነባው አካዳሚ ዋና አላማው የባለሀብቶችን ትምህርት፣ የፋይናንስ እውቀትን ማጎልበት እና በገበያ ውስጥ አቅምን ማሳደግ ነው። የአካዳሚው ጅማሮ በሚቀጥለው ወር ስራ እንዲጀምር እቅድ ለተያዘለት የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ቅድመ ዝግጅት አንድ አካል ሲሆን ይህም ኩባንያው የመማር እና የንግድ እድሎችን ለማስፋፋት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አካዳሚ እያደረገ ያለው ድጋፍ፤

ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ አካዳሚውን በማቋቋም የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዘመናዊ የበይነ መረብ ትምህርት መድረክን በማዘጋጀት እና በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን በማሳተፍ አጠቃላይ የኮርስ ሞጁሎች እንዲዘጋጁ አስችሏል። በተጨማሪም አሳታፊ የሞጁል ይዘት፣ የኮርስ ቪዲዮዎችን እና የማማሪያ ጥያቄዎች ያካተተ የለርኒንግ ማኔጅመንት ሲስተም በመዘርጋት የተሳታፊውን ፍላጎት ባማከለ መልኩ በራስ የሚመራ የስልጠና ስርዓትን ይይዛል። ይህም ለዲጂታል ስርዓት ቅድሚያ የሰጠ የስልጠና መንገድ ከተማሪዎች እስከ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ያሉ ተሳታፊዎችን ምቹ እና ለሁሉም ተደራሽ በሆነ መንገድ ስለ ካፒታል ገበያ መሰረታዊ እውቀትን እንዲጨብጡ ያስችላል።

ስለኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አካዳሚ፤

አካዳሚው በካፒታል ገበያ ጽንሰ-ሀሳብ ላይ የተቀናጀ እና ቀጣይነት ያለው ትምህርት በተለያዩ የስልጠና መንገዶች በማቅረብ የካፒታል ገበያውን እድገት ለመደገፍ ያለንን ተነሳሽነት ማሳያ ነው። የአካዳሚው ኮርሶች በጀማሪ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ተብለው በሚጠሩ ሦስት ደረጃዎች የተከፋፈሉ ሲሆን፤ ይህም ሰልጣኞች በራሳቸው ፍጥነት እና ፍላጎት መሰረት ስልጠናውን እንዲወስዱ ያስችላቸዋል።

አሁን በይፋ የተጀመረው የጀማሪ ደረጃ ስልጠና እንደ የካፒታል ገበያ መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳቦች፣ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ዋና ተግባራት፣ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች፣ የህግ ማዕቀፎች፣ የሸሪዓ ህግጋትን የሚያሟሉ ሰነደ ሙዓለንዋዮች፣ የካፒታል ማሳደግን እና የኢንቨስትመንት ስልቶችን በማካተት በአስር ሞጁሎች ተዘጋጅቶ ቀርቧል። የጀማሪ ደረጃ ስልጠናው ከክፍያ ነፃ የሚሰጥ ሲሆን የቀረቡትን 10 መድብሎች ላጠናቀቀ የስልጠና ምስክር ወረቀትንም አካቶ ቀርቧል። ይህም ስለ ካፒታል ገበያ ለማወቅ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች የህብረተሰቡ አካላት እንደ ግብዓትነት ያገለግላል። ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች በሚከተለው ማስፈንጠሪያ በመግባት ለስልጠናው መመዝገብ ይችላሉ :esxacademy.com.

መግለጫዎች፤

ጥላሁን እስማኤል ካሳሁን (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ፤ “የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አካዳሚ መጀመር በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ በእውቀት የሰለጠነ የካፒታል ገበያ ተሳታፊዎችን ለመገንባት ያለንን ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ጅምር ማሳያ ነው። ተደራሽ እና በሞጁል የተደራጀ ስልጠና በመስጠት የግለሰቦችን አቅም ከማጎልበትም ባሻገር በሃገሪቱ የበለፀገ የካፒታል ገበያ ስነ-ምህዳር ግንባታን እያጠናከርን እንገኛለን”

ወ/ሮ ሂክመት አብደላ፤ የኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክለውም፤ “ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ በዚህ ፈር ቀዳጅ ስራ ላይ ከኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ ጋር አብሮ በመስራቱ ክብር ይሰማዋል። አካዳሚው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት የሚደግፍ፣ አካታች እና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ዘርፍ በማበልፀግ ሂደት ውስጥ ከምናቀርበው ድጋፍ ጋር የተሳሰረ ነው። ይህ አካዳሚ በሃገሪቱ ያሉ ግለሰቦች እና ቢዝነሶች ላይ ያለውን አወንታዊ ተፅዕኖ ለማየት ከፍተኛ ፍላጎት አለን።”

ስለ ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ፤

ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ አካታች እና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ዘርፍ በማጎልበት የሰው ሃይልን እና የምጣኔ ሃብት ግንባታ መደገፍ ላይ እየሰራ ይገኛል። በተጨማሪም፤ ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ግለሰቦች እና ቢዝነሶች ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኝ ውጤታማ የፋይናንስ ዘርፍ ለመገንባት ይሰራል።

############

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ እራሱን በራሱ የሚቆጣጠር ድርጅት እና ዋና የገበያ አስተባባሪ በመሆን የተቋቋመ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ ነው። የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ የካፒታል ተደራሽነትን ማጎልበት እና ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እድገት አስተዋፅዖ ማድረግን ዋና አላማው በማድረግ የተማከለ የአክሲዮን፣ የእዳ እና የአማራጭ ሰነዶች መገበያያ መድረኮችን ያቀርባል።